የሃይማኖት ጸሎት /The Creed - የኦርቶዶክሳዊያን አለማቅፋዊ የጋራ ጸሎት


 

ኹሉን በያዘ፣ ሰማይንና ምድርን፥ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ፡ አንድ አምላክ በሚኾን፡ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።
ዓለም ሳይፈጠር፡ ከእርሱ ጋራ በነበረ፥ አንድ የአብ ልጅ፥ አንድ ጌታ በሚኾን፡ በእግዚአብሔር ወልድም እናምናለን። እርሱም፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፥ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፥ የተወለደ እንጂ፡ ያልተፈጠረ፣ በመለኮቱ፡ ከአብ ጋራ የሚተካከል፣ ኹሉ፡ በእርሱ የኾነው፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በሰማይ ካለው፣ በምድርም ካለው፡ ያለእርሱ፡ ምንም ምን፡ የኾነ የለም።
ስለእኛ ስለሰዎች፥ እኛን ለማዳን፡ ከሰማይ ወረደ፤ በመንፈስ ቅዱስ ግብር፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም፡ ከሥጋዋ፡ ሥጋ፥ ከነፍሷ፡ ነፍስ ነሥቶ፡ ፍጹም ሰውን ኾነ። በጴንጤናዊው ጲላጦስ ዘመን፡ ስለእኛ፡ መከራን ተቀበለ። ተሰቀለ። ሞተ። ተቀበረ። በሦስተኛውም ቀን፡ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። በክብር፥ በምስጋና፡ ወደሰማይ ዐረገ። በአባቱም ቀኝ፡ በዙፋኑ ተቀመጠ። ዳግመኛም፡ በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ፡ በምስጋና ይመለሳል። ለመንግሥቱ፡ ፍጻሜ የለውም።
በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እርሱም፡ ሕይወትን የሚሰጥ፣ ከአብ የሠረፀና በነቢያት ዐድሮ የተናገረው፥ በሓዋርያት ላይ የወረደውና በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት፡ ዓለሙን፡ በጸጋው የሞላው፡ ቅዱሱ የእውነት መንፈስ ነው። ለእርሱም፡ ከአብና ከወልድ ጋራ፡ በአንድነት እንሰግድለታለን፤ እናመሰግነዋለንም።
በአንዲት ቅድስት ካቶሊክ እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ኃጢኣት በሚሠረይባት፡ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።
በሙታን ትንሣኤ፥ በዘለዓለምም ሕይወት እናምናለን። ለዘለዓለሙ፤ አሜን።